የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
26/02/2014 ዓ. ም
መቱ ዩኒቨርሲቲ በጎሬ ከተማ ያሰራውን የተቀናጀ የከተማ ግብርና የአትክልትና የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ፡፡ ፕሮጀክቱ የተሰራው በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማራማሪዎች ሲሆን የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ሴቶች ኑሮ ለማሻሻልና ለመደገፍ ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ የተቀናጀ የቴክኖሎጂ የከተማ ግብርና በውስጡ በትንሽ ቦታ ላይ የአትክልትና የዶሮ ዕርባታ ያካተተ ነው፡፡

ፕሬጀክቱን የሰሩት የመቱ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች መ/ር ሀብታሙ መንግስቱና ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ ታደሰ እንደተናገሩት ይህ የተቀናጀ የከተማ ግብርና በአካባቢው አዲስ ከመሆኑም ባሻገር በትንሽ መሬት ላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማምረት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱም 16 በማሕበር የተደራጁ ሴቶች ታቅፈው ተጠቃሚ እንደሆኑ ለመረዳት ተችለዋል፡፡ ይህንን ፕሮጅከት ለመስራት ከ340000 ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡

በርክክብ ወቅትም የአሌ ወረዳ አስተዳዳሪና የወረዳው የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ጉብኝት ተደርጓል፡፡

በርክክብ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የመቱ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በድሉ ተካ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በምርምር ያገኛቸው ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ በማስተላለፍ ለሀገራችን ዕድገት የራሱን አሻራ እንደሚወጣ ገልጸው በቀጣይም ሌሎች ስራዎችን በተመሳሳይ ለማህበረሰቡ ያደርሳል፡፡ ሆኖም ግን ተሰርተው የሚተላለፉትን መሰል ፕሮጀክቶች ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት እንድከባከቡ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ርክክብ ወቅት የአሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደበሌ ዘውዴ እንደተናገሩት ወረዳው ይህንን ዕድል በማግኙቱ ዩኒቨርሲቲውን አመስግነው ተሰርተው በማህበር ለተደራጁ ሴቶች የተላለፈውን ፕሮጀክት በሚያስፈለጉው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉና ተሞክሮውን በከተማው እንድስፋፋ እንደሚሰሩ ተናግዋል፡፡

በማህበር ተደራጅተው የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች እንደተናገሩት ከዚህ የተቀናጀ የተክኖሎጂ የከተማ ግብርና በርትተው በመስራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፅው መቱ ዩኒቨርሲቲም ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.