ህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ሐምሌ 5/2013
መቱ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም አዲስ ተመድበው ወደ ግቢው ለመጡ ከ 3000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎቹ ኦረንቴሽን ሰጠ።
መቱ ዩኒቨርሲቲ 2004 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ተመድበው ለሚመጡ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል በማድረግ ተማሪዎቹ ከአካባቢ ማህበረሰብ ባህልና ወግ ጋር ቶሎ እንዲተዋወቁ፤ በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ፍፁም ባይተዋርነት ሳይሰማቸው መፈጸም ስለሚገባቸው መብትና ግዴታዎች ቀድሞ ግንዛቤ በመስጠት ተማሪዎቹ ይበልጥ የእንግዳነት ስሜት እንዳይሰማቸው የማድረግ ልምድ እንዳለው ይታወቃል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዘንድሮ በ2013ዓ.ም በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው ለመጡ ከ3000 በላይ ለሚሆኑ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።
በኦረንቴሽኑ መግቢያ ላይ የመቱ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተካልኝ ቀጄላ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በሰላም በመምጣታቸው የተሰማቸው ደስታ በመግለጽ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል። አያይዘውም ቀደም ሲል የነበሩ አጋጣሚዎችን በመጥቀስ እንዲሁም ስለ ዩኒቨርስቲው አጭር ገለፃ የሰጡ ሲሆን አዲስ ገቢ ተማሪዎችም በየዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ስለሚጠበቅባቸው መብትና ግዴታዎች ጠንቅቀው ከወዲሁ ሊያውቁት እንደሚገባና ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ያሳሰቡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሁሉም ነገር ከጎናቸው መሆኑንም ለተማሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡
በገለፃ ጊዜውም በዩኒቨርሲቲው ከተማሪ አገልግሎት ጋር ይበልጥ ተያያዥነት ያላቸው የሥራ ክፍሎች ለተማሪዎች የሚሰጡ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሬጅስትራር አገልግሎትን አስመልክቶ፤ በተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ፣ የግሬድ አያያዝ፣ የትምህርት ከፍል መረጣ ወዘተ፣ በቤተ-መጻህፍትና ዶክመንቴሽን አጠቃቀም፤ በሴቶች፤ ህጻናትና ወጣቶች አገልግሎት፣ ኤች አይቪና ተዛማጅ በሽታዎችን በተመለከተ፣ በተማሪዎች ህብረት ዙሪያ እንዲሁም ስለ አጠቃላይ የግቢ ደህንነት ጉዳዮች ላይ አጠር ያለ ገለጻ እና ጠቃሚ መልዕክቶች ቀርቦላቸዋል ፡፡
በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ማከናወን ስላለባቸው ተግባራት በቂ ግንዛቤ ከኦረንቴሽኑ እንዳገኙ በፕሮግራሙ የተሳተፉ ያነጋገርናቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገልፆልናል።
Join us on:
https://t.me/mettuniversity

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.