የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ግንቦት 03/2014 ዓ. ም
መቱ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ. ም በትምህርት ሚኒስተር የተመደቡትን ከ4500 በላይ ተማሪዎች እየተቀበለ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለ2014 ዓ. ም በትምህርት ሚኒስተር አዲስ የተመደቡትን ተማሪዎች በደማቅ ስነ ስርዓት እየተቀበለ ይገኛል፡፡ በዚህ የቅበላ ስነ ስርዓት ላይ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ዳይሬክቶሬቶች ዲኖች፣ መምህራ፣ ሰራተኞች፣ እንዲሁም የመቱ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ፋንታዬ አሰፋን ጨምሮ አባ ገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡ ዶ/ር ለታ ዴሬሳ የመቱ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ አዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው የመጡትን ተማሪዎች እንኳን ወደ ውቧ፣ አሬንጓዴና የሰላም ተምሳሌት የሆነች ከተማ በሰላም በደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ መቱ ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን ትውልድን የመቅረፅ ኃላፊነቱን ለመወጣት በትጋት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ አግባብ አዲስ ተመድበው የመጡትን ተማሪዎች ለማብቃት እንሰራለን ብለዋል፡፡ለዚህም ደግሞ አዲስ ተመድበው ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የመጡት ማሳያዎቻችን ናቸው ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የመቱ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተካልኝ ቀጄላ ባስተላለፉት መልዕክት እንኳን ወደ ሰላማዊና ውቧ አሬንጓዴ መቱ ዩኒቨርሲቲ በደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ መቱ ዩኒቨርሲቲ ምቹና ሰላማዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመሆኑ እንደ ሀገር የተጣለበትን ዜጋን የማብቃት ስራ ለማሳካት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውድና ብርቅዬ ተማሪዎችን ለማገልገል በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በሁሉም የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ ፋንታዬ አሰፋ ባስተላለፉት መልዕክት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለትምህርት ወደ መቱ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተመድበው የመጡትን ተማሪዎች በቆይታቸው በከተማው ውስጥ ምንም የፀጥታ ስጋት ሳይገባቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተናግረው፤ ዛሬ የተቀበልናቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው በጥሩ ውጤት አጠናቀው መርቀናቸው ወደ ቀጣይ የህይወት ምዕራፍ እንደምንሸኛቸው ተስፋ አደርጋለውና በምርቃታችሁ እንገናኝ ብለዋል፡፡ በዚህ የቅበላ ስነስርኣት ላይ አባ ገዳዎችና የኃይማኖት አባቶችም አባታዊ መልዕክትና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መቱ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱም ካምፓሶቹ ከ4500 በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እንደሚበቀል ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.