በመቱ ዩኒቨርሲቲ “በሀገር ግምባታ የምሁራን ሚና” በሚል ርዕስ የምሁራን የውይይት መድረክ ተካሄደ፡:
26/04/2015 (ህ.ው.ግ.ዳ)
የውይይቱ ዋና አላማ ምሁራን የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ በተሟላ መልኩ ተገንዘበዉ በሀገር ግንባታና እድገት ውስጥ ምሁራዊ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና መንግስትና ምሁራን ይበልጥ ተቀራርበዉ የሚሰሩበትን መደላድል መፍጠር መሆኑን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር እንደገና አበበ ገልፀዋል፡፡ ውይይቱ በሁለቱም ካምፓሶቻችን ለሶስት ተካታታይ ቀናት በ 2 ደረጃ ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን በመጀመርያዉ ቀን የዩኒቨርሲቲዉ ካውንስል አባላት ብቻ የተሳተፉበት መድረክ ሆኖ በሁለተኛዉና በሶስተኛዉ ቀን የዩኒቨርሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላት፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ የት/ት ክፍል ሀላፊዎች፣ አስተባባሪዎች፣ ቡድን መሪዎች፣ ሁሉም መ/ራንና የቴክኒካል ረዳቶች የተሳተፉበት ሰፊ መድረክ ተካሂዷል፡፡ ሂደቱም የውይይት መነሻ ገለፃ ከቀረበ በኋላ በቡድን ውይይቶች ተደርገዉ ከየቡድን ውይይቱ የተነሱት አንኳር ሀሳቦችና ጥያቄዎች የዩኒቨርሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሞገስ ባልቻ፣ ክቡር አቶ እንዳልካቸዉ ተፈሪና ዶ/ር እንደገና አበበ በተገኙበት የማጠቃላይ መድረክ ላይ ቀርቦ ማጠቃለያ ተሰጥቶበታል፡፡
በውይይቱ ባለፉት 4 አመታት የተገኙት ስኬቶች የተብራሩ ሲሆን አሁን የውስጥና የውጭ ጫናዎች፣ ከጅኦ ፖለቲካችን ጋር ተያይዘዉ ያሉ ጉዳዮች፣ የውሃ ፖለቲካ፣ የፖለቲካዉ ገበያና አሻጥሮች፣ የድል ሽሚያ፣ ክራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች፣ የዓለም ሚዲያ ጫና፣ ጦርነትና በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች፣ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት፣ የኑሮ ውድነቱ፣ ዓለም አቀፋዊ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ወዘተ እንደ ሀገር የተደቀኑብን አደጋዎች መሆናቸዉ ተገልጧል፡፡ እነዚህ ውስብስብ ችግሮች የሀገር ግምባታና እድገት ላይ ትልቅ ተፅኖ ያላቸዉ መሆኑን እንዲሁም የዓለምን የሀይል ሚዛን በሚገባ በመረዳት ምሁራን እውቀታቸዉን በመጠቀም ምርምሮችን በማድረግ እነዚህን ችግሮች ቀርፈን ዘላቂ ሠላምን በማስፈን ሀገርን የምንገነባበትና እድገትን የምናመጣበትን በሳል ሀሳቦች በማፍለቅ ለመንግስት ምክረ-ሀሳብ ማቅረብ እንዳለባቸዉ፤ መንግስትም ደግሞ ከምሁራን ጋር አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑ ተገልጧል፡፡ እውቀት የሀገር እድገት መሰረት እንደ መሆኑ የምሁራን ሚና በሀገር ግምባታ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዳለዉ ተጠቅሶ ምሁራን የሚያነሷቸዉን ጥያቄዎችም መንግስት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በመጨረሻም መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የወሰደዉን የሰላም አማራጭ በየትኛዉም የሀገሪቱ ክፍል ለሚፈጠሩ ግጭቶችም ተመሳሳይ የሰላም አማራጭ ለመዉሰድ ዝግጁ መሆኑንና ለዚህም የምሁራን ሚና ትልቅ መሆኑም ተገልጧል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.