ተሻሻሉ የቁም እንሰሳት ትራንስፎርሜሽን ፕሮጅክት አውደ ጥናት ተካሄደ፡፡
መቱ ዩኒቨርሲቲ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ለ10 ዓመት ለመተገበር የተጀመረውን የተሻሻሉ የቁም እንሰሳት ትራንስፎርሜሽን ፕሮጅክት የማሳያ አውደ ጥናት አካሄደ።
ህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት: ሚያዚያ 6/2014ዓ.ም
የማሳያ አወደ ጥናቱ በመቱ ዩኒቨርሲቲ በደሌ ካምፓስ የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዞን እና ወረዳ ሃላፊዎች፣ የክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብትና የእንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኤጄንሲ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና መምህራን ተገኝተውበታል።
በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አወደ ጥናቱን የከፈቱት የበደሌ ካምፓስ ዲን ዶ/ር ኦዳ ግዛው እንዳሉት በኢትዮጵያ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ ከሆነው የግብርና ዘርፍ ውስጥ የእንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ በማዘመን መሰራት እንዳለበት ያወሱት ሲሆን፤ በዚህ አውደ ጥናትም ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰራ ያለውን የቁም እንስሳት ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ባለድርሻ አካላትን በአንድነት በማሰባሰብ ፕሮጀክቱ ያሉበትን ሂደት፣ ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች መለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ኦዳ በንግግራቸው አክለውም በዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን በፕሮጀክቱ የተሰሩት ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
በማሳያ አውደ ጥናቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር እንደገና አበበ እንደገለፁት መቱ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ዘርፉ በመንግስት የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከእነዚህ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ውስጥም በአካባቢው የቁም እንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከኬዴራልና ከክልል መንግስታት፣ በየክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በየአካባቢው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር የወተትና የስጋ ምርትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ዶ/ር እንደገና አበበ አክለውም፣ በቡኖ በደሌ እና በኢሉ አባቦር ዞኖች በቴክኖሎጂ የተደገፈው የተሸሻሉ የቁም እንሰሳት ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሲሆን በዚህ አወደ ጥናትም በፕሮጀክቱ የደረሱበትን ደረጃ በማቅረብ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ ብዙ ልምዶች እንደተገኙበትም ገልጸዋል፡፡
የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ትስስር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር በድሉ ተካ በአውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ እንደተናገሩት ሀገራችን በቁም እንስሳት ሀብት ቀዳሚ ደረጃ ላይ ብትሆንም በተፈለገው ልክ ግን በቅንጅት ባለመሰራቱ ተጠቃሚነቱ እምብዛም እንደሆነ የገለፁ ሲሆን አሁን ግን የተጀመረው ስራ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በጋራ እና በቅንጅት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.