የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዩኒቨርሲቲያችን ከተቋቋመ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከአስተዳደር እና ከአካዳሚክ ክንፉ ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲውንን ለሀገር ዓቀፍ እና ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በዋናነት የዩኒቨርሲቲአችንን ገጽታ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለውን መስተጋብር የሚያጠናክሩ ስራዎችን ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ጋር በመተባበር የሚሰራና እየሰራ ያለ ሲሆን ከዚህን በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲአችን ከሀገር ውስጥና እና ዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር ግንኙነቶች የመፈጠርና የተፈጠሩ ግንኙነቶችም የማጠናከር ስራን እየሰራ ያለ የስራ ክፍል ነው፡፡

የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ከላይ ከተረዘሩት ስራዎች በተጨማሪም የስራ ክፍሎች የሚያደርጉትን የስራ ዕንቅስቃሴዎች፣ በትምህርት ዘርፉም መምህራን የሚሰሩትን የፈጠራ እና የምርምር ስራዎች በቅርበት በመከታተል የሚዲያ ሽፋን የመስጠት እና መረጃዎችንም በማጠናከር በዩኒቨርሲቲአችን ማህበራዊ ትስስር ሚዲያ እና ድረ ገጽ ላይ በመቀቅል መረጃዎችን ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ ያደርጋል፡፡

በዩኒቨርሲቲያችን ትኩረት የሚሹ የተለያዩ ውስንነቶች ቢስተዋሉም በለውጥ ሂደት ላይ ያለ እና የምስረታውን የ10ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን በ2004 ዓ.ም ሲመሰረት 300 መደበኛ ተማሪዎችን በመቱ መምህራን ኮሌጅ ተቀብሎ መማር ማሰተማር የጀመረ ሲሆን ባለፉት ሰባት ዙሮችም ከ10,000 በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ20,000 በላይ ተማሪዎችን በመቀበል በ47 የመጀመሪያ ድግሪ እና በ28 የሁለተኛ ድግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ስድስት የምርምር ጣቢያዎችን በተለያዩ ወረዳዎች በማቋቋም የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን የሚደግፉ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ያለ እና ለወደፊትም አሁን ካለው በተጠናከረ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ አቅዶ እየሰራ ያለ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከ8 ሚሊዪን ብር በላይ ወጪ በማውጣትም የማህበረሰቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ማህበረሰብ ተኮር ኤፍ ኤም ሬዲዮ በማቋቋም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የአከባቢውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፍላገት ለሟሟላት በአካባቢው የመጀመሪያ የሆነውን ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመገንባት በሂደት ላይ ያለ ሲሆን በዞኑ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችንም በውድድር በመቀበል በዋናው ግቢ በ2013 ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራውን ጀምሯል።

ዩኒቨርሲቲያችን በ2013 የትምህርት ዘመንም በተለያዩ መርሀ ግብሮች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የነበሩ ከ2800 በላይ ተማሪዎችን ለ8ኛ ዙር በመጀሪያ እና በሁለተኛ ድግሪ በደማቅ ሁኔታ ለማስመረቅ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ በመሆኑ ለመላው የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦች፣ መመህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ከወዲሁ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታችንን እናስተላልፋልን፡፡

አዲሱ ዓመት 2014 ዓ.ም የሰላምና የጤና እንዲሆንልን እንዲሁም በዩኒቨርስቲያችን ያቀድነውን ስራ ምናሳካበት የሰኬት ዓመት እንዲሆንልን ለመላው የዩኒቨርስቲያችን ማህበረሰብ እንመኛለን ።

የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.