የመቱ ዩኒቨርሲቲ የመጽሐፍት ማሰባሰብና የ2ኛ ደረጃ ልዩ ትምህርት ቤት የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነስርዓት አካሄደ፡፡
የመጽሐፍት ማሰባሰብ ስነ ስርዓቱ የተካሄደው እንደክልል የተጀመረውን ፕሮግራም መሰረት በማድረግ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ ከ10200 በላይ መጻሐፍቶች ለማሰባሰብ ተችለዋል፡፡ መጽሐፍቶችን የለገሱ የመቱ ዩኒቨርሲቲ እና የተለያዩ የአካባቢው ማህበረሰብ ናቸው፡፡ በዚህ የመጽሐፍት ማሰባሰብ ስነ ስረዓት ላይ የተገኙት የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር እንደገና አበበ፣ የኢሉ አባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መኮንን ባይሳና የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ቀልቤሳ ቶሌራ ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር እንደገና አበበ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዉ ከሚሰጠው የመማር ማስተማር ጎንለጎን ከስር የሚመጣ ትውልድ በትምህርቱ ብቁ እንዲሆን በሚያስፈልገው ሁሉ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የተለገሱት መጻሐፍትንም የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ቀልቤሳ ቶሌራ ለዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ትስስር ምክትል ፕሬዝዳንት ለሆኑት ለረ/ት ፕሮፌሰር ፀጋዬ በርኬሳ ያስረከቡ ሲሆን በዶ/ር ሚካኤል ብራዲ መታሰብያ የህዝብ ቤተመጽሐፍት በከተማው ለወጣቶች የንባብ ባህል ለማሳደግ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው 2ኛ ደረጃ ልዩ ት/ቤት ለመሥራት መሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ለማሰራት ካቀዳቸው አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር እንደገና አበበ ስለትምህርት ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ ከ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ በየዓመት 240 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚጀምርና በቀጣይ አራት ዓመት 1000 ተማሪዎችን ከዞኑ በትምህርታቸው በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን በማወዳደር ተቀብሎ በራሱ እንደሚያስተምር ገልጸዋል፡፡
የትምርህት ቤቱ መሰረተ ድንጋይም በመቱ ከተማ በዶ/ር ሚኤካል ብራዲ መታሰብያ የህዝብ ቤተመጽሐፍት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተቀምጧል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.