የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት (ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም) መቱ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ፓወር ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባባበር የሳይንስ፣ቴክኖሎጂ፣ኢንጂነሪንግና ሂሳብ (ስቴም) ማዕከል ለታዳጊ ተማሪዎች ከፍቷል፡፡ በማዕከሉ የኮምፒዉተር ቤተ-ሙከራና የኤሌክተሮኒክስ ቤተ-ሙከራ ሙሉ ግብዓት ተሟልቶለት የተደራጀ ሲሆን በዛሬዉ እለት ተመርቋል፡፡ ተማሪዎች በዘመናዊ መንገድ በተደራጀ ቤተ-ሙከራ መማራቸው የፈጠራ ስራን እንደሚያበረታታ የገለፁት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር እንደገና አበበ ማዕከሉ በመቱ ከተማና በአካባቢው የሚገኙ ልጆች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር በመደገፍ የፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ምቹ ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም ማዕከሉ የፈጠራ ስራን ስለሚያበረታታ ዘመኑን የዋጁና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበቁ ተመራማሪዎችን በማፍራት ሀገር ለመለወጥ አጋዥ ሚና አለው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲዉ ልዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች በበዴሌና በኢሉ አባቦር ዞኖች ያሉ ተማሪዎች ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ስኬትማ ለመሆን መልካም ስነ-ምግባርን መጎናፀፍ፤ አቅማቸዉን አሟጠዉ በመማር በቂ እውቀትና ክህሎት መጨበጥ እንዲሁም ባለ ራዕይ መሆን እንደለባቸዉ ዶ/ር እንደገና መክረዋል፡፡ የስቴም ፓወር ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ አንተነህ ፍሰሃ በበኩላቸው ድርጅታቸው ማዕከሉን በማደራጀት ሳይወሰን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ዘላቂ ድጋፍ በተጨማሪ የሳይንስ ቤተ-ሙከራ እንደሚያያስፋፋ ገልፀዋል፡፡መዕከሉን ለማቋቋም 6 ሚሊየን የሚገመት ወጪ የተደረገበት ሲሆን ይኸዉም የቨርችዋል የኮንፒተርና የኤሌክትሮኒክስ ቤተ-ሙከራ ቂሳቁስ በተጨማሪ ፈርኒቸርና ኦፕሬሽን በጀት ያካትታል ብለዋል። የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እሼቱ ችሎ በበኩላቸዉ የፈጠራ ክህሎትና ዝንባሌ ያላቸዉ ተማሪዎችበበዴሌና በኢሉ አባቦር ዞኖች እየተመረጡ ክረምት ክረምት በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ላይ ስልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡ ማዕከሉ ሲከፈት የተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ማዕከሉን የጎበኙ ሲሆን ስለማዕከሉም ማብራሪያና ገለፃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ We are dedicated to serve the community!

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.