የተማሪዎች ምርቃት
መስከረም 9/2014

መቱ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች 2260  ተማሪዎችን አስመረቀ።
መቱ ዩኒቨርስቲ ለ8ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በመቱ እና በበደሌ ካምፖስ የሚማሩ 2260 ተማሪዎችን በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ድግሪ በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመረቀ።

በዕለቱ ከተመረቁት 2260 ተመራቂዎች 116 በሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን 794 ደግሞ ሴት ተመራቂዎች መሆናቸው ታውቋል።.

መቱ ዩኒቨርስቲ በ5 ኮሌጆች እና በአንድ ትምህርት ቤት በ37 የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የትምህርት ቴክኖሎጂ እና መረጃ አስተዳደር (Educational Technology and Information Management) የትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን ማስመረቅ ችሏል።

በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር እንደገና አበበ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገራችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ ችግር እና ውጣ ውረዶችን አለፋችሁ እዚህ ታሪካዊ ቀን የደረሳችሁ ባለ ድሎች በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል። አክለውም ተመራቂዎች በተማሩበት ሙያ እንዲሁም እንደ አንድ ዜጋ በሀገራችን የተጋረጠውን በውስጥ እና በውጭ የተከፈተውን የዲጂታል ዘመቻ በመመከት እንዲሁም በሙያችሁ በስነምግባር እና በታማኝነት ሀገራችሁን ለማገልገል ዝግጁ መሆን አለባችሁ ሲሉ ለተመራቂዎቹ መልዕክት አስተላልፏል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግዳነት የተገኙት የዩኒቨርስቲው ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢፌዲሪ የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሃላፊ የሆኑት ክቡር አቶ ሞገስ ባልቻ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዚህ ፍፁም ሰላማዊ፣ ለኑሮ ተስማሚ እና አረንጓዴ በሆነው በለምለሚቷ ኢሉ አባ ቦር እንዲሁም በዚህ ውብ በሆነው ግቢ ተምራችሁ የልፋታችሁን ፍሬ ለማየት በመብቃታችሁ ደስታችሁ እጥፍ ድረብ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። አክለውም በተማራችሁበት ሙያ በስራ ላይ በምትሰማሩበት መስክ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሻሻል በሚያገለግሉ የጥናት እና ምርምር ስራዎች ላይ በትጋት እንድትሳተፉ እንዲሁም በተሰማራችሁበት ሁሉ ህዝባችሁንም በቅንነት እና በታማኝነት እንድታገለግሉ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በተጨማሪም አሁን ሀገራችን እየገጠማት ላለው ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የተማረ የሰው በመሆኑ የዛሬ ዕለት ተመራቂዎችም ለችግሮች የመፍትሔ አካል በመሆን ሀገራዊ ግዴታችወን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በዕለቱ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የእውቅና ሰርተፊኬት እና የተለያዩ ሽልማቶ የተበረከተ ሲሆን ከነዚህም በመቱ ካምፖስ ተማሪ ዲሮ ቶሎሳ ግቡ
ከትምህርት ቴክኖሎጂ እና መረጃ አስተዳደር (Educational Technology and Information Management) የትምህርት ክፍል 3.98 አጠቃላይ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ እና ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳ የተረከበ ሲሆን በበደሌ ካምፓስ ደግሞ ተማሪ ገዙ ከተማ ጫካ ባጠቃላይ ውጤት 4:00 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
ዘገባው: የህዝብ እና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬ

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.