በ ACEP የተሠሩ ፕሮጀክቶችን የማስመረቁ ስራ ቀጥሏል
መስከረም 24/2016 ዓ.ም (ህ.ው.ግ.ዳ)
በመቱ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የMPH የድህረ-ምረቃ ዕጩ ምሩቃን ተማሪዎች በ ACEP በቡሬ ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብን በማሳተፍ ያስገነቡት የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያና ማስወገጃ ፕሮጀክት የዩኒቨርሲቲዉ የአካደሚክ ም/ፕ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሳቢት ዜይኑ፣ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ተሾመ በቃና፣ የቡሬ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አድማሱ ተስፋዬ፣ የቡሬ ወረዳ አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ካሳሁን አየለ እና ሌሎችም አካላት በተገኙበት ደማቅ የምርቃትና የርክክብና መርሃ-ግብር ተደርጓል፡፡ የቡሬ ወረዳ አስተዳዳሪ ተወካይ ዩኒቨርሲቲዉ በከተማቸዉ በሰራዉ ፕሮጀክት መደሰታቸዉን ገለፀዉ ለዚህ ስራ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን በሙሉ አመስግነዋል፡፡ የከተማዉ ከንቲባ ተወካይ በበኩላቸዉ ስለተሰራዉ ችግር ፈቺ ስራ አድናቆትና ምስጋናቸዉን ከገለፁ በኋላ ፕሮጅክቱ ለታለመለት አላማ ይውል ዘንድ ከከተማዉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን በህብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰሩ፤ ስራ አጦችን በማደራጀት ወደ ስራ እንደሚያስገቡና ከወረዳዉ የግብርና ቢሮ ጋር በመሆን ከደረቅ ቆሻሻዉ ቃጠሎ የሚገኘዉን አመድ እንደ ማዳበርያ የምንጠቀምበት አግባብ ላይ አጠናክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡ አቶ ሳቢት ዜይኑ በበኩላቸዉ ዩኒቨርሲቲዉ እንደ መሪ ቃሉ በመማር ማስተማሩ፣ በጥናትና ምርምሩ፣ እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎቱ ዘርፍ በትጋት ህብረተሰቡን እያገለገለ ሲሆን ለወደፊትም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ አቶ ሳቢት አክለዉም ይህ ፕሮጀክት ህብረተሰባችንን እያገለገልን መሆኑን ከሚያሳዩ ስራዎች አንዱ ሲሆን የከተማዉ አስተዳደር ለከተማዉ ማህበረሰብ ምቹና ፅዱ ከተማን ለመፍጠር ለሚያደርገዉ ጥረት በጎ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የACEPን ፍልስፍና በሁሉም ኮሌጆቻችን ለማስጀመር እየሰራን ነዉ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተሸመ በቃና በበኩላቸዉ የኮሌጁ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በACEP ፅንሰ-ሀሳብ መሠረት ለምርቃት ማሟያነት በተጨባጭ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ በርካታ ፕሮጀክቶችን በጋምቤላ ከተማ፣ በኢሉ አባቦርና በቡኖ በደሌ ዞኖች ሲሰሩ መቆየታቸዉን ጠቅሰዉ የዛሬዉ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ምረቃም የዚሁ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህብረተሰብ ጤና ት/ት ክፍል ሀላፊ አቶ ቀኖ መልካሙ በበኩላቸዉ ተማሪዎቻቸዉ ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዉ ፕሮጀክቱ በብዙ ልፋትና ድካም ተሰርቶ እውን የሆነ በመሆኑ ለታለመለት አላማ በአግባቡ ይውል ዘንድ የከተማ መስተዳድሩና ህብረተሰቡ ሀላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡
Mattu University
Dedicated to serve the community!






Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.