የህዝብና ውጪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት፤ ጥቅምት 12/2014 ዓ/ም
የመቱ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት አደረጉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ዕቀድ (2013-2022) ከዚህ በፊት አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ውይይቱ የተካሄደው የዕቅዱን እስካሁን አፈጻጸምና ጊዜው ከሚጠይቀው ጋር እንዴት አቀናጅተው ዕቅዱን ማስፈጸም በሚቻልበት ነው፡፡ በዚሁም መሰረት የአስሩ ዓመቱ ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመ/ር መሐመድ ረሻድ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡ በተደረገ ውይይትም በየደረጃው ያሉት አመራሮች በተለይ ከማስፈጸም አቅም ጋር ተያይዘው በሁሉም የዩኒቨርሲቲው አካላት ዘንድ በቁርጠኝነት መነሳሳት እንዲኖር መስራት እንዳለባቸው አፀንኦት ተሰጥተው ተወያይተዋል፡፡
በመቀጠልም በህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መ/ር አስረሳኸኝ ኃ/መስቀል አመራርነትና ተቋማዊ ግንኙነት (Leadership and Organisational Communication) በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል፡፡ መ/ር አስረሳኸኝ በፀሑፋቸውም በዓለም ላይ ያለውን ነባራዊ አመራርነትና ተቋማዊ ግንኙነት ፅንሰ ሃሳብ ምን እንደሚመስልና ከዩኒቨርሲቲያችን አንፃር እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ እንዴት ተጠቅመንበት ለውጥ ልናመጣበት እንደምንችል የተለያዩ ነጥቦች አንስተዋል፡፡
በዚህ የውይት መድረክ ላይ ተገኙት ዶ/ር እንደገና አበበ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የአስር ዓመቱን ስትራቴጅክ ዕቅድ ሲዘጋጅ የዩኒቨርሲቲውንና የሀገራችን የዕድገት ፍላጎት መሰረት አድርጎ የተጋጀ ነው ብለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት እያንዳንዱ አመራር በየዘርፉ ያሉትን አመራሮች በማንቀሳቀስ ለለውጥ እንዲተጉ እንዲሁም ያለውን የግቢው የስራ ባህል ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ አሳስበዋል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.