ህዳር 17/2015( የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት)
መቱ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ጋር በመተባበር “ሰላማዊ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ”/“Peaceful University Community’’ በሚል ርዕስ ከተማሪዎች ጋር የህዝብ ውይይት መድረክ አካሄደ፡፡
የውይይቱ ዋና አላማ ተማሪዎች ለሰላም ትልቅ ቦታ እንዲሰጡና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን እንዲያዳብሩ ማስቻል ሲሆን ይህ ደግሞ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ መሰረት እንደ ሆነ ከመድረኩ ለማወቅ ተችለዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር እንደገና አበበ እንደተናገሩት ሰላም የአለም ህዝብ ሁሉ አጥብቆ የሚፈልገዉ እሴት ቢሆንም አሁንም አለም በሰላም እጦት እንደምትሰቃይ ገልፀዉ ሰላም ስለፈለግነዉ ብቻ የምናገኘዉ ሳይሆን ሰላም ከእራስ የሚጀምር ሆኖ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማዳበር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለዉም እንዲህ አይነቱ መድረክ ተማሪዎች መወያየትን እሴታቸዉ እንዲያደርጉ የሚረዳ በመሆኑ ለመደረኩ መመቻቸት የኢትዮጵያ ሰላም ተቋምን ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር በመተባበር መድረኩ እንዲመቻች በማደረጉ አመስግነዉ ተማሪዎቹም በውይይቱ ላይ በትኩረት እንዲሳተፉና በግቢው ውስጥም ሆነ በማንኛውም ቦታ ለሰላም መስፈን የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የውይይት የመነሻ ፅሁፍ የጂማ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በዶ/ር እውነቱ ሀይሉ ቀርቦ ተማሪዎች ውይይት ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ለሁለት ተከታታይ ቀናትም ለዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎች ህብረትና ለሠላም ፎረም ሠላምን አስመልክቶ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.