መቱ ዩኒቨርሲቲ ለ1ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የጾታዊ ጥቃት መከላከልና የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ሰጠ
 Published Date: Oct 28, 2026
Share:

መቱ ዩኒቨርሲቲ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ አዘጋጅነት ለዩኒቨርሲቲው የ1ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች ሲሰጥ የቆየውን የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ የጾታዊ ጥቃት መከላከልና የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከተካሄደ በኋላ ዛሬ አጠናቋል። በመክፈቻ ንግግራቸው የሥራ አስፈጻሚው ኃላፊ ወ/ሮ ሲሳይ ተፈሪ ተማሪዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ፣ ሥልጠናው ለግል ደህንነታቸው፣ ለግል እድገታቸውና ለትምህርት ስኬታቸው ያለውን ጠቀሜታ በማብራራት በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

ሥልጠናው ተማሪዎቹ ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ስለ HIV/AIDS መከላከል፣ ስለማይፈለግ እርግዝና መከላከያ ዘዴዎችና ስለ ኃላፊነት የተሞላ ውሳኔ አሰጣጥ ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ ያለመ ነው። በተጨማሪም የጾታዊ ጥቃትን መለየትና መከላከል፣ የግል ደህንነትን መጠበቅ፣ የተጎጂዎችን መብት ማክበርና አስፈላጊ ሲሆን ተገቢውን የድጋፍ አገልግሎት መፈለግ በሥልጠናው ከተካተቱ ዋና ዋና ርዕሶች መካከል ይገኙበታል።

በተመሳሳይ፣ ራስን ማወቅ፣ ግልጽ ራዕይና ግብ ማስቀመጥ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ ውጤታማ የአጠናን ዘዴዎችን መተግበር፣ ጫናን መቆጣጠርና የአቻ ግፊትን በጥበብ መቋቋም የሕይወት ክህሎት ሥልጠናው ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው። በተለይም ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው አዲስ የትምህርትና የኑሮ አካባቢ ለተቀላቀሉ የ1ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች፣ የግል ኃላፊነትን በመወጣት፣ ከሚያዘናጉ ተጽዕኖዎች በመጠበቅና ትምህርታቸውን በቅድሚያ በመያዝ የወደፊት ራዕያቸውን እንዲያሳኩ ማገዝ የሥልጠናው ዋና ዓላማ ነው። ተማሪዎቹ ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ መቱ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት፣ በግንዛቤ ፈጠራና በድጋፍ አገልግሎቶች ሁሌም ከጎናቸው እንደሚቆም ያረጋግጣል።

Gallery

Recent News

© 2026 Mattu University. All Rights Reserved.